1439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በኢ.ሶ.ክ. በደማቅ ተከብሮ 911 የሕግ ታራሚዎችም በምህረት ተፈቱዋል

ጅግጅጋ (Cakaaranews)አርብ፤ሰኔ 08/2010ዓ.ም 1439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላ ሃገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል። በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ ሚሰጠውና በድምቀት የሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። የእስልምና እምነት ተከታዮች የሃይማኖት አባቶችና በመሺዎች የሚቆጠሩ የከተሟ ነዋሪዎች የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች በአንድነት በመሆን በጅግጅጋ ስታዲዮም የኢድ ሶላትና ሌሎችም ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ተፈፅመዋል።

በስነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ፕረዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር  በክልሉ፣ በሃገሪቷና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ የሕግ ታራሚዎችን በተለያዩ ጊዜያት በምህረት እንዲፈቱ ከማድረጉም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በክልሉ ስለነበረው የሰላም እጦት ምክንያት በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ከ15ሺህ በላይ ታራሚዎች ይገኙ እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ግን 1612 ብቻ እስረኞች እንዳሉ ጠቁመው ከእነዚህም መካከል የኢድ አልፈጥር በዓል የፍቅር፣ የይቅርታና የበረከት በዓል እንደመሆኑና ይቅር መባባል የክልሉ ባህል እንደመሆኑ መጠን በዛሬው እለትም 911 የሕግ ታራሚዎች በምህረት ፈቱዋል።

መላው የክልሉ ሕዝብ ከክልሉ መንግሥት ጎን ተሰልፎ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሠላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር የተመዘገቡትን ዘርፈ-ብዙ መልካም ውጤቶች አሁንም እንዲደገሙ በክልሉ ሁለንተናዊ ተሳተፏቸውንና አስተዋጿቸውን ከምን ጊዜውም በላይ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ  ክቡርፕረዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ አብዱራህማን ሀሰን ሁሴን በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ጾም ወቅት ሲፈፅማቸው የነበሩ መልካም ተግባራትን አጠናክሮ እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በበዓሉ አከባበር ስነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ሙስሊሞች በረመዳን ጾም ወቅት በጎ ሥራዎችን በመሥራት በጾም እና በፀሎት ማሳለፋቸውን ጠቁመው በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ከዘመድ ወዳጅና ጎረቤቶቻቸው ጋር በፍቅርና በደስታ እያከበሩ እንደሚያሳልፉም ገልፀዋል።

በመጨረሻም 1439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በክልሉ ዞኖች፤ወረዳዎችና የከተማ መስተዳደሮችም በፍቅር፤በሠላምና በአማረ መልኩ ተከብሮ ውሏል።