በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኤምባሲ ድጋፍ በኢትዮጵያ ሶማሌ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባላሙያዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት ስልጠና አዘጋጀ

ጅግጀጋ(Cakaaranews)ማክሰኞ፤ሰኔ 12/2010ዓ.ም በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኤምባሲ ድጋፍ የሚደረግለትና በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሞያን ለመደገፍ ታስቦ በተዘጋጀ ውድድር ላይ ተሳታፊዎችን ለማብቃት የተዘጋጀ ስልጠና በዘሬው እለት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ መካሄዱ ተገለፀ። በስልጠናው ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የክልሉ ሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎችም ተሳትፈዋል።

በተጨማሪም በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረገው እና በሃገር አቀፍ ደረጃ የጋዜጠኞችን ሞያ ለመደገፍ ብሎም የክህሎት ውድድርን ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ስልጠና የምርመራ ጋዜጠኝነትን በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ ለማደረግ የሚያስችል ክህሎት በማሳደግ የጋዜጠኞችን ሞያና አቅም የማበልፀግ አላማ እንዳለውም የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገልጿል። በዚህ ስልጠና ላይ ጋዜጠኞች የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት USAID እና የአሜሪካን መንግሥት የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል CDC በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስለሚካሄዱት የሥራ እንቅስቃሴ ግንዛቤ በማስጨበጥ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ የጋዜጠኝነት ሞያን ተከትለው የምርመራ ዘገባ እንዲሰሩ ታስቦም የተዘጋጀ ነው።

በመድረኩ ላይም የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈርሃን መሀሙድ፤የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ኢንጅኔር ኢድሪስ እስማኢል እንድሁም የክልሉ ሚዲያና የኮሙኒኬሽን አመራርና ባላሙያዎችም ተካፈለዋል።በስልጠናው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት   በክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ኢንጅኔር ኢድሪስ እስማኢል አብዲ  "በቅድሚያም ሁላችሁም እዚህ የተገኛችሁትን እያመሰገንኩ ይህ ስልጠና በመዘጋጀቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ስልጠናው በልማት ጋዜጠኝነት ላይ የልምድ ማጎለበቻ መሆኑን እየገለፅኩ በአቅም ግንባታ ስልጠናው የሚሳተፉ ጋዜጠኞች ከስልጠናው በልማት እና በምርመራ ጋዜጠኝነት ብዙ ልምድ ይቀስማሉ ይህም ለሚዲያ ባለሞያዎች ትልቅ ጠቃሜታን ያበረክታል። ከዚህምበተጨማሪ  በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የፕሬስ ነፃነት በመጠቀም የክልሉ ሚዲያ ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ የሠላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ብሎም የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎችን ለህዝብ በማድረስ በህዝብ እና መንግሥት መካከል አገናኝ ድልድይ በመሆን የተጣለባቸው ሃላፊነት ይበልጥ እንዲወጡ የሚያስችላቸውም ነው። እንደሚታወቀው የክልላችን መንግሥት የማህበረሠቡን የሚዲያ አማራጮችን በማስፋፋት ከሚኒ ሚዲያ ጀምሮ እስከ ትላልቅ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ማሰራጫዎች ተደራሽነትን እያስፋፋ ይገኛል። እነዚህ ተቋማትም ፈጣንና ወቅታዊ መረጃዎችን ወደ ሕዝቡ በማድረሱ ረገድ ስኬታማ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ። በመጨረሻም ስልጠናውን ያዘጋጁትን የአሜሪካን ኤምባሲ አካላትን እያመሰገንኩ የስልጠናው ተሳታፊዎችም ስልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስባለሁ"  ሲሉ ተናግሯል።

በመጨረሻም ፕሮጀክቱ ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት በመጀመሪያው ክፍል ከየክልሉ ለተውጣጡና በሥራ ላይ ከሚገኙ ጋዜጠኞች ጋር ለሁለት ቀናት የሚቆይ ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል ይህም በጤና፣ ትምህርትና ግብርና ብሎም ሠብዓዊ እርዳታን በመሳሰሉት የልማት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የምርመራ ዘገባን መስራት የሚያስችሉ ክህሎቶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይሆናል።  በሁለተኛው ክፍል ተሳታፊ ጋዜጠኞች በክልላቸው ልማት ተኮር ዘገባን በመሥራት በሃገር ዓቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ውድድር ላይ እንዲሳተፉና ተጨባጭ የሆኑ ዘገባዎች እንዲያቀርቡ የሚያግዝ መሆኑን የስልጠናው አዘጋጆች ገልፀዋል።