ከጅግጅጋ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተመረቁ 445 የጤና ባለሞያዎች በእጣ አወጣጥ የሥራ ምደባ ሥነ ስረዓት ተደረገ

ጅግጅጋ(Cakaaranews)፤ሰኔ 15/2010ዓ.ም  በቅርቡ ከጅግጅጋ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተመረቁ የጤና ባለሞያዎች የሥራ ምደባ እና እጣ አወጣጥ ሥነ ስረዓት መደረጉ ተገለፀ። በእጣ ማውጣቱ እና የቅጥር ክወና ሥነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር የተገኙ ሲሆን የእጣ ማወጣቱ ሥነ ስርዓትም በእያንዳንዱ ባለሞያ በእራሱ እጅ እንደተከናወነ የክልሉ መንግስት ገለፀ።

የጅግጅጋ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅርቡ በተለያዩ የሞያ ዓይነቶች ያስመረቃቸውን 445 የጤና ባለሞያዎች በክልል፣ በዞን እና በወረዳ በሚገኙ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላዎች እራሳቸው በሚያወጡት የቅጥርና የምደባ ቦታን የማወቅ ሥነ ስርዓት በጅግጅጋ ከተማ ቀርያን ዶዳን የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄዱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።

በመድረኩ ላይም የየኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት  ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሃሙድ ኡመር፤ተመራቂዎቹና የተለያዩ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። ከዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርዓቱ በኋለም የጤና ባለሞያዎቹ የቅጥር ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል።

በተጨማሪም ክቡር ፕሬዝዳንቱ ለባለሞያዎቹ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱን አስመልክተው ፍትሃዊና ግልፅ ሂደቱን ባደረጉት ንግግር  "በተወሰነ መልኩ ስለ ዕጣ አወጣጠ ሥርዓቱ የተወሰኑ ነጥቦችን አነሳለሁ ምክንያቱም የተወሰኑ ማህበረሠባችን ውስጥ ትንሸ ግርታ አለና በመጀመሪያ የተከናወነው ሥራ የተመረቁበትን ሞያ እና ያሉትን ክፍተቶች ማጤን ነበር። በመቀጠልም በአዋላጅ ነርስ የተመረቁ ወንድም ሴትም ብዛታቸውን እና በዚህ ላይ ክፍተት ያለባቸው ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ይጣራሉ ይህም መለያ ኮድ ደሞዝ እና ቦታው በግልፅ የተቀመጠበት ነው። ይህን ስል ምናልባትም እናንተ በግልፅ ትረዱታላችሁ ነገር ግን የተለያዩ መረዳት ያልቻሉ ሠዎች የዕጣ እና ምድብ አወጣጥ ሥርዓትን ባለመረዳት አልያም ልምድ ሆኖባቸው ተቀምጠው ያልሆነውን እንዲህ ሆነ ለሚሉ በግልፅ እንዲረዱት ስለሚያስፈልግ ነው። አንዳንድ ጊዜ እኮ እዚህ ጠረጴዛ ላይ ወረቀት አስቀምጣችሁ በዓይኑ እያየ አይደለም የለም  የሚል ይኖራል። ስለዚህ የሠውን ልጅ በመጀመሪያ የሚያሳምነው ትክክለኛ እና ግልፅ የሆነ አሠራር ነው። በዚህም መሠረት ሁሉም እንደ የተማረበት ሞያ ጤና ቢሮም መቀበል በሚችለው አቅሙ ሁሉም የሚፈለግበትን ያሟላ በመሆኑ አንተ እዚህ ሂድ አንተ ደግሞ እዛ ሂድ ብሎ ማለቱ ፍትሃዊ ባለመሆኑ ልክ እንደ ዛሬው በግልፅ እያንዳንዱ ባላሙያ የሚደርሰውን ቦታ በእጁ ያወጣል ይሄ ደግሞ ግለሰቦች በሃሜት እንዲህ ተደረገብኝ ብለው እንዳይሉ ግልፀኝነትን ያሰፍናል። ሌላው አደራ ለማለት የምፈልገው በየደረሳችሁ ምድብ ቦታ ስትሄዱ የተጣለባችሁን የሞያ አደራ መንግሥት ስለቀጠራችሁ ወይም ፕሬዝዳንቱ ስለተናገራችሁ ሳይሆን በሞያዊ ሥነ ምግባርና ህዝብን የማገልገል ስሜት፣ በቅንነትና በታማኝነት እንዲሁም የተቀላጠፈ አገልግሎት እንድትሰጡ አሳሰባለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

በተያያዜም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊ አቶ አይደሩስ አህመድ የተሳካ እና ግልፅ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርዓት እንደነበር ገልፀው በቀጣይም ለጤና ባለሞያዎቹ አሰፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውና ሁሉም ወደ የሥራ ቦታቸው በመሄድ የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ባለሞያዎቹ በበኩላቸው በዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርዓቱ ደስተኛ መሆናቸውን በመግልጽ ወደ ተመደቡበት የሥራ ቦታም በመሄድ የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡም ገልፀዋል።