የኢ.ሶ.ክ ፕሬዝዳንት ከኢለሌ የነዳጅ ምርቃት በኋላ ከተለያዩ የህብረተሠብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ መሆኑ ተገለፀ

ጅግጅጋ(Cakaaranews)ረቡዕ፤ሰኔ 27/2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ  በሸቤሌ፣ ቀራሄይ፣ ጀረር እና ዶሎ ዞኖች ሥር በሚገኙ 12 አከባቢዎች እንደሚገኝ የተረጋገጠ ሲሆን አሁን በፖሊ ጂሲ ኤል ኩባንያ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ቁፋሮ የሚደረግባቸው ቦታዎች ግን በሁለት የክልሉ ዞኖች ውስጥ እንደሆነ የሚታወቅ ከመሆኑ ባሻገር የድፍድፍ ነዳጅ የወጣባቸው የቆራሄይ እና ሸበሌ ዞኖች ሲሆኑ በዚህ ሳምንት ድፍድፍ ነዳጅ የተገኘበት አካባቢ የኢሊሌ ድፍድፍ ነዳጅ ከሸበሌ ዞን ዋና ከተማ ጎዴይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በቆራሄይ ዞንም የተፈጥሮ ጋዝ የተገኙባቸው በርካታ አካባቢዎች እንዳሉ ሆኖ በዶበወይን ወረዳ ስር የሚገኘው ጄህዲን/ካሉብ ድፍድፍ ነዳጅ በኢፌዴሪ የማዕድን፣ ተፈጥሮ ጋዝና ፔትሮልየም ሚኒስትርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ መመረቁ ይታወሳል።

ከነዳጅ ቁፋሮው እና መገኘት በተጨማሪ መነሳት ያለበት ትልቁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ እያደረጉ ያሉት በክልሉ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች በመዘዋወር የነዳጁን መገኘት አስመልክቶ ከየአካባቢው ማህበረሠብ ጋር ቆይታ ማድረግ እንደሆነም ተገልጿል። የነገው የክልሉ እና የሃገራችን ብሩህ ተስፋሳ ከመሆኑ ባሻገር የተገኙ የልማት ውጤቶችን በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም  ክቡር ፕሬዝዳንቱ ለህዝባቸው ያስገነዘቡበት ቆይታም እንደነበራቸው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገልጿል።

በተለይ ደግሞ በዚህ የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተገኘውን የማህበረሠብ ክፍል በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች በመገኘት የተዘጋጀውን የድፍድፍ ነዳጅ ናሙና በማሳየት ህዝቡን ሲያበስሩት እንደነበረም የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አክሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ክቡር ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደምም እንደሚያደርጉት ሁሉ የአካባቢውን ህብረተሠብ የተገኘውን የተፈጥሮ ሃብት አስመልክተው በዝርዝር እና በግልፅ ሲያወያዩ እንደነበረም መንግስት አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር ከኢሊሌ የነዳጅ ጉድጓዶች መመረቅ ጋር በተያያዘ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች በመዘዋወር የአካባቢውን ማህበረሠብ እያወያዩ እንደሆነ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። በተያያዘም  ፕሬዝዳንቱ በኢለሌ፣ በዶበወይን ፣በቀብሪደሀር ፣በሼኮሽ ፣በደጋህቡር እና በአራርሶ ወረዳዎች የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ከቀብሪበያህ ከተማ አስተዳድር እና ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር ለውይይት መገናኘታቸውም ታውቀዋል።  

በቅርቡ የተመረቀውን የኢሊሌ ነዳጅ በማስመልከት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር በክልሉ ወረዳዎች  ቆይታቸው  ከሁሉም የአካባቢው ሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ወጣቶች ፣ሴቶች ፣የክልሉ ጸጥታ አካላት እና የሚመለከታቸውን በአጠቃላይ ሲያወያዩ መቆየታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪምፕሬዝዳንቱ  በሁሉም የክልሉ ከተሞች ሲደርሱ በአካባቢው ነዋሪዎች በሚደረግላቸው ደማቅ አቀባበል እጅግ ደሰታኛ መሆናቸውን ገልጸው የጉዟቸው ዋና አላማ በቅርቡ የተመረቀው የኢለሌ ነዳጅ ከመሆኑ ባለፈ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች የተገኘውን ሰላም እና ልማት ማጠናከር መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የአካባቢውን ወጣቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው የማህበረሠብ ክፍሎችን የሚያወያዩ ሲሆን የድህነት ቀንበር የሚሰበርበት እና ድህነትን ታሪክ የምናደርግበት ጊዜ እሩቅ እንዳልሆነም ፕረዝዳንት አብዲ መሀሙድ ለአከባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል። በተያያዜም መጪው ጊዜ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሃገር ብሩህ እንደሚሆንም ፕረዝዳንቱ አስታውቀዋል። በቀጣይም የክልሉ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በትኩረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ክቡር ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

በመጨረሻም የክቡር ፕሬዝዳንቱ ጉዞ ከነዳጅ መገኘት በዘለል ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ከሠላም ጋር በተያያዘ የተለየ ፀጉረ ልውጥ በአካባቢው እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከተገኘ ህብረተሠቡ በአስቸኳይ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል የማሳወቅ ሃላፊነት እና የአካባቢውንም ሠላም የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።