በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአንድ ቀን ግንባታ ያለቀው ህንፃ ተገኘ

ሻይጎሽ(cakaaranews)አርብ᎓ሰኔ 29/2010ዓ.ም. በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ለጦር መሪው ለማርሻል ግራዚያኒ ፅ/ቤት በአንድ ቀን የተሠራ ታሪካዊ ቤት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሸይጎሽ ወረዳ በሆነችው በሻይጎሽ ከተማ ይገኛል። እ.ኤ.አ በ1937 ዓ.ም የፋሺስት ጣሊያን መንግሥት ለ2ተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ለመውረር ባደረገችው እንቅስቃሴ የምስራቁ የሃገራችን ክፍል የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢን በተቀመጠበት ጊዜ ለአስተዳደር እንዲያመቸው የተለያዩ ግንባታዎችን እንዳከናወነ ይታወሳል።

በወቅቱ በፋሺስት ጣሊያን መንግሥት ከተሠሩት ህንፃዎች አንዱ በቆራሄይ ዞን ᎓ሻይጎሽ ወረዳ በአንድ ቀን ውስጥ አልያም በ24 ሠዓታት ውስጥ የተሠራው ህንፃ ይገኝበታል። ይህ ቅርስ ከክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ በ295 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው በሻይጎሽ ላይ በአንድ ቀን ውስጥ እንደተሠራ የሚነገርለት ህንፃው ለጊዜው ጦር መሪ ለማርሻል ግራዚያኒ ፅ/ቤት ታስቦ የተሠራና ለተወሰነ ጊዜም ግራዚያኒ እንደተገለገለበት ዛሬም በህይወት ያሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች ይናገራሉ።

ህንፃው ሙሉ በሙሉ በድንጋይ እና ሲሚንቶ የተሠራ ከመሆኑም በተጨማሪ የበረንዳው ቋሚ ከትላልቅ ወጥ ድንጋዮች የተገጣጠመ እና ምንም አይነት ብረት በህንፃው ጥቅም ላይ እንዳልዋለም ይገለፃል። የሃገር ሽማግሌዎቹ እንደሚሉት  ይህ በወረዳዋ የሚገኘው የማርሻል ግራዚያኒ ፅ/ቤት በአንድ ቀን ተሠርቶ ሊጠናቀቅ የቻለበት ምክንያት በርካታ የሰው ኃይል እና ባለሞያዎች የተሳተፉበት መሆኑንም አውስተዋል። በዚህም ይህ ታሪካዊ ህንፃው በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት አገልግሎት የማይሠጥ ሲሆን ካለው ታሪካዊ ዳራ እና እድሜ አንፃር የሚመለከተው አካል የቅርስ ጥበቃና ከለላ ቢያደርግለት ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ መሆን እንደሚችል ለመጠቆምም እንወዳለን።