በጅጅጋ ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትናና ሥራ ፈጠራ ኤጀንሲ ለ65 ባለሞያዎች ስልጣና መስጠቱ ተገለፀ

ጅግጅጋ(Cakaaranews)ሰኞ᎓ሐመሌ 02/2010ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መዲና በሆነችው የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትና እና ሥራ ፈጠራ ኤጀንሲ ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ከተለያዩ ቀበሌዎች ለተውጣጡ 65 ሰልጣኞች በምግብ ዋስትና እና ሥራ ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ ታስቦ ስልጠና እንደተሰጠ ተገለፀ።በተጨማሪም ኑሯቸውን ለማሻሻል እንዲያስችላቸው ብሎም ዕውቀትና የኮሙኒኬሽን ክህሎታቸውን ለማሳደግ እንዲረዳ የታሰበ ስልጠናም መሆኑ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዲአዚዝ መሃድ  ገልጿል።

ከስልጠናዉ በኋላ የጅግጅጋ ከተማ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ካሊድ አብድራህማን እና የጅግጅጋ የከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዲአዚዝ መሃድ ስልጠናዉን አስመልክተው ለክልሉ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት  የስልጠናውን አላማ  አቅመ አናሳ የሆኑ የማህበረሠቡ አባላት ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እንዲሁም በምግብ ዋስትና እራሳቸውን ያልቻሉትን ለማገዝ እና ለመደገፍ የታሰበ እንደሆነም ገልጿል።

በተጨማሪም የስልጠናው አዘጋጆችና አስተባባሪዎች ሰልጣኞቹ ከስልጠናው ባገኙት እውቀትና ልምድ በአካባቢያቸው የሚኖሩትን አቅመ አናሳ እና በምግብ ዋስትና እራሳቸውን መደገፍ ያልቻሉ የማህበረሠብ ክፍሎችን በዘላቂ የምግብ ዋስትና ችግራቸውን እንዲፈቱ ለማስቻልና የኑሮ ዘይቤያቸውን ለማሻሻል እንዲረዷቸው የታሰበ እንደሆነም አክለዋል።

በአጠቃላይ ከሃገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ በከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም የታቀፉ 11 ከተሞች የተመረጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የጅግጅጋ ከተማ አንዷ ሲትሆን በዚህ ፕሮግራም በአጠቃላይ ወደ 10,000 (አስር ሺህ) የሚጠጉ ሰዎች በቀጥታ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም  ኃላፊዎቹ ገልጿል።