7ተኛው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት መደበኛ ጉባኤ በዛሬ ዕለት በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ተጀመረ

ጅግጅጋ (cakaaranews)ረቡዕ፤ሐምሌ 04/2010ዓ.ም  5ተኛው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት 3ተኛ የሥራ ዘመን 7ተኛው መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጅግጅጋ ከተማ የተጀመረ ሲሆን በጉባኤው ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት የፓርቲ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መሀመድረሺድ ኢሳቅ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕረዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር፣ የክልሉ ም/ቤት አባላት እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ መሀመድረሺድ ኢሳቅ የጉባኤው አጀንዳ የሆኑትን የ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ማጽደቅ፣ የ2011 በጀት ዓመት እቅድ  ማጽደቅ፤የኦዲትና የፍትህ  አካላት ሪፖርት በማጽደቅ እና ሌሎች የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ለም/ቤቱ አባላት ለውይይት አቅርቧል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሶማሌ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር የ2010ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርቱ ላይም በዋኝነት በመሠረተ ልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች በሰፊው ማብራሪያ ሰጥተውበታል። አያይዘውም በ2010 በጀት ዓመት በክልሉ ግብርና ምርት እና ምርታማነት፣ በወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት የተሠሩ ሥራዎችን ሪፖርት በማቅረብ የምርክር ቤት አባላቱ በሁሉም ዘርፎች በቀረበው ሪፖርት እንዲወያዩ እና አስታየት እንዲሰጡ ክቡር ፕረዝዳንቱ ጠይቀዋል።

ከዚህ በመተጨማሪም የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀሙድ ሁሉንም በፌዴራል መንግሥት የተከናወኑ ተጨባጭ ለውጦች ባጭሩ በመዳሰስ፤ በኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዶ/ር አህመድ የተገኘውን ይቅርባይነት፣ አንድነት፣ መፈቃቀርና የመደመር ሥራዎች እንደ ክልል በተጨማሪም እንደ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) ዋና አጀንዳ አድርጎ በቁርጠኝነት እንደሚያስቀጥሉም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ክቡር ፕረዝዳንቱ እንደ መንግሥትም እንደ ድርጅትም ለመላው የክልሉ ህዝብ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን ከመንግሥት እና ከድርጅትም ጥፋት ለፈጸሙት ሁሉ ይቅርታ ከጠየቁ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

ፕረዝዳንት አብዲ መሀሙድ ኡመር በቅርቡ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦብነግ(ኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር) ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ የተሰረዙበት ውሳኔ የክልሉ መንግሥት እና የክልሉ መሪ ድርጅት ኢሶህዴፓ በጽኑ እንደሚቀበል እና በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ አንድም የኦብነግ አባል የሆነ ግለሰብ እንደለሌ በመግለፅ ሁሉም የኦብነግ አባላት በይቅርታ ከህዝቡ ጋር እንደሚቀላቀሉም አክለው ገልፀዋል።

በተመሳሳይም ሁሉም የኦብነግ አባላት እንደሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች በሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው የይቅር ባይነት እና የመደመር ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት በክልሉ የሚገኙ እስር ቤቶች ሁሉ እንዲዘጉ ታቅዶ እየተንቀሳቀሰ ከመሆኑ በዘለል ለታራሚዎች ይወጣ የነበረው በጀትም ለመሠረተ ልማት እንደሚዞርም ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር በክልሉ የወጣው የተፈጥሮ ጋዝና ድፍድፍ ነዳጅ ለመላው የሃገሪቱ ብሎም ለክልሉ ህዝብ የእድገት ድል መሆኑን ጠቅሰው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ያስመዘገቡት ተጨባጭ ለውጦች የሚደነቁ ከመሆናቸውም ባሻገር ማንም የማይክዳቸው ሃቅ መሆናቸውን ፕረዝዳንቱ አብራርተዋል።

ፕረዝዳንቱ አሁን ባለንበት ጊዜ ውሽት እና ፕሮፖጋንዳ ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ከመሆኑም በተጨማሪ የክልሉ ህዝብ ነቅቶ ወደ ልማት የዞረበት፤ አንድነት የፈጠረበት ብሎም ሁሉም የመደመር ጉዞ ላይ መሆኑንም ገልፀል።

በመጨረሻም 7ተኛው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት መደበኛ ጉባኤ በቀጣይ ቀናት እንደሚሄድም አፈ ጉባኤው አቶ መሀመድረሺድ ኢሳቅ አስታውቀዋል።