በኢ.ሶ.ክ ጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው የክልሉ ማዕከላዊ ማረሚያ ቤት ተዘግቶ ቦታው ለመስጊድ በመስጠት በማረሚያ ቤቱ የነበሩ ሁሉም የህግ ታራሚዎችም በይቅርታ ተለቋል

ጅግጅጋ(Cakaaranews)ሐሙስ፤ሐምሌ 05/2010ዓ.ም በኢ.ሶ.ክ.መ ጅግጅጋ ከተማ የሚገኙው የክልሉ ማዕከላዊ ማረሚያ ቤት ውስጥ የነበሩ ሁሉም የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀው ወደ ህብረተሠቡ እንዲቀላቀሉ ከመደረጉም በተጨማሪ በማረሚያ ቤትነት ሲያገለግል የቆየው ይህ ስፍራ የአምልኮትና ልማት ማዕከልነት  እንዲሆን በክልሉ መንግሥት በመወሰኑ ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ከክልሉ መንግሥት ጎን ተሰልፈው በሃገሪቱ እየተከወኑ የሚገኙትን የሠላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ከዳር ለማድረስ ብሎም ለማስቀጠል ከክልሉ መንግሥት ጋር በጋራ ወደ እድገት ለመሠማራት መወሰናቸውም ገለጹ።

ከዚህ ቀደም በዚህ ክልል ውስጥ በሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የህግ ታራሚዎች  ይገኙበት የነበረ ሲሆን በተለያዩ የእምነትና የጋራ በዓላት ወቅት የክልሉ ፕሬዝዳንት ከክልሉ ፍትህ አካላት ጋር በመተባበር እስረኞችን በይቅርታ መለቀቃቸውን ይታወሳል። በቅርቡ በተከበረው የኢድ አል ፈጥር በዓል ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ባርካታ የህግ ታራሚዎችን በምህረት ለቆ፤የቀሩትን የህግ ታራሚዎች በቀጣይ ወደ ህብረተሠቡ እንዲቀላቀሉ ለማደረግ ቃል በገቡት ቃል መሠረት በአሁኑ ጊዜ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ መቻላቸውም ገልጿል። በተጨማሪም በክቡር ፕሬዝዳንቱ የማረሚያ ቤቱ ሥፍራ በቀጣይ ለመስጊድ እና ለወጣቶች የክህሎት ማሳደጊያ ማዕከል የሚገነባበት ሥፍራ እንደሚሆንም ተገልጿል።

በጅግጅጋ ከተማ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር ማረሚያ ቤቱን በመዝጋታቸውና  አጠቃላይ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከመልቀቃቸው በተጨማሪ ማረሚያ ቤቱ ህብረተሠቡን የሚጠቅም የልማት ማዕከል እንደሚገነባበት በሰሙ ጊዜ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ ማረሚያ ቤት የነበሩ የህግ ታራሚዎች በቆይታቸው የተለያዩ  መደበኛ ስልጠናዎችና የሞያ ትምህርት ሲሰጣቸው እንደነበረም አስታውቀዋል።በቀጣይም ከህብረተሠቡ ጋር በመሆን ከማረሚያ ቤቱ ባገኙት ዕውቀትና ሞያ ከመንግሥት ጎን በመቆም ወደ ልማት ሥራዎች እንደሚሠማሩም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።