የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሞ ክልሎች በአጎራባች አካባቢዎቻቸው የፌዴራል የፀጥታ አካላት ገብተው የማረጋጋት ሥራ እንዲሠሩ ተስማሙ

አዲስ አበባ(cakaaranews)ሰኞ፤ሐምሌ 9/2010 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የፌዴራል የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ ገብተው የሠላምና መረጋጋት ሥራ እንዲሠሩ ተስማሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አልፎ አልፎ የሚታየውን የዜጎች ሕይወት መጥፋት እንዲቆም፣ ይህንን የሚያባብሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ በአጠቃላይ አሁን የተፈጠረውን ብሩህ ተስፋ ለማስቀጠል በፍቅርና አብሮነት ሕዝቡ እንዲተጋ፤ ከዚህ በተቃራኒው የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለመከላከል የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ሕግ የማስከበር ሥራቸውን በሃላፊነት ስሜት እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን መመሪያ ተከትሎም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመርና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም ግጭት በተፈጠረባቸው አጎራባች አካባቢዎች የፌዴራል የፀጥታ ኃይል በመግባት የጸጥታ፣ የሠላምና መረጋጋት ሥራ እንዲሠራ፤ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ መስማማታቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ለሚዲያ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ለአፈጻጸሙ የሁለቱም ክልል የመንግሥት መዋቅሮች ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚወጡ ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ማረጋገጣቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል።

በተለይ የሕግ‑ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራና የሁለቱም ክልል ሕዝብ እንደወትሮው የለውጥ ሂደቱን በመጠበቅ ለመፍትሄው ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ በበርካታ እሴቶች የተሳሰረውን የሁለቱ ክልል ሕዝብ ከመሰል ግጭቶች በመከላከል ለዘላቂ መፍትሄ፣ ለሠላምና ፍቅር አብሮ የሚሠራበትን ሁኔታ ለማስቀጠል ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፍረንሶችን በአፋጣኝ ለማካሄድም ርዕሰ መስተዳድሮቹ መወሰናቸውም ሚኒስትሩ አክሏል።