በ2010 ዓ.ም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ ዝግጅት ተደረላቸው

አዲስአበባ(cakaaranews)ረቡዕ፤ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጅ ለሆኑ ከአዲስ አበባና ሌሎች የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የ2010 ዓ.ም ተመራቂዎች የተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች አዲስ አበባ ተገኝተው የእንኳን ደስ አላችሁ ዝግጅት ማድረጋቸው ተገለፀ። እነዚህ የዘንድሮ ተመራቂዎች ቁጥራቸው 143 ሲሆን በተለያዩ የትምህርት መስኮች መመረቃቸውን የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ጽ/ቤት አስታውቋል።

በተጨማሪም ከተመራቂ ተማሪዎች መካከልም 32ቱ በህክምና ዶክትሬት የተመረቁ ሲሆን 7ቱ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ መሆኑም ተገልጿል። ክልሉ ባዘጋጀው በዚህ ደማቅ የእንኳን ደስ ያላችሁ ዝግጅት ላይ የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ከድር አብዲ እስማኤል፣ የክልሉ መስተዳደር ጽ/ቤት ም/ሃላፊ አቶ አብዲወሊ ሐጂ መሀመድ፣ከክልሉ የተመረጡ የኢፈዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አካላት እንዲሁም የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውም ተገልጿል።

በሌላ በኩል በእለቱ ለተመራቂዎቹ የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቶ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከደር አብዲ እስማኤል “በመጀመሪያ ሁላችሁም ለዚህች የደስታ ቀን እንኳን አደረሳችሁ፣ ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻችሁም እንኳን ደስ ያላችሁ እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሎም ክልላችን በፈጣን የለውጥና እድገት ጎዳና ላይ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪም ዘርፈብዙ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እየተከወኑ የሚገኝ ከመሆኑም በዘለለ ከዓመት ዓመት ወደ የተለያዩ ከፍተኛ የት/ት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል በሌላ በኩልም ክልላችን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ  የተማረ ሰው ሃይል በማፍራት ወጣቶችን በተለያዩ የስራ መስኮች በማመቻቸት  ላይ ይገኛል። ለዚህም ክልሉ በትምህርቱ ዘርፍ እየሰጠ የሚገኘውን ትኩረት ማሳየት የሚያስችል ሲሆን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች፤ክልሉ እያከናወናቸው የሚገኙ ዘላቂ ሠላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች በቅንነት ለማስቀጠል እናንተም የዛሬ ተመራቂዎች ያስተማራችሁን ህዝብ በቅንነትና ሃላፊነት ለማገልገል የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ይጠበቅባችኋል።” ሲሉ ለተመራቂዎቹ መልዕክታቸውን አስተላለፏል።

በተመሳሳይም  የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መስተዳደር ጽ/ቤት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ  ም/ሃላፊ  አቶ አብዲወሊ ሐጂ መሀመድ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላለፏል።

በተያያዘም በአዲስ አበባ የኢሶህዴፓ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ በበኩላቸው “የኢ.ሶ.ክ ልዩ ድጋፍ ከሚሹ ክልሎች መካከል በፈጣን እድገት፤ልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች አስመልክቶ  የክልሉ መሪ ድርጅት ኢሶህዴፓ ባሳየው ተጨባጭ ለውጥ ክልሉ እራሱን ከልዩ ድጋፍ ሊያወጣ የቻለ ክልል በመሆኑ የዚህ የፈጣን ልማትና እድገት ለማስቀጠል የበኩላችሁ እንድትወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።” ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች መልዕክታቸውን አስተላለፏል።

በመጨረሻም ተመራቂ ተማሪዎቹ የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ በሃላፊነት እንደሚወጡና ክልሉ ብሎም ሃገሪቱ በያዘችው የፈጣን ልማት ሥራዎች ላይ የበኩላቸውን ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።