የኢ.ሶ.ክ.መ ም/ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ በደንበል ወረዳ አራቢ ቀበሌ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መርቀው መክፈታቸው ተገለፀ

ደንበል(cakaaranews)ረቡዕ፤ሐምሌ 19/2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀምዲ አደን የሚመራ፤ በፌዴራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ማዕድን ኢነርጂና ደን ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ መውሊድ ሃይር፣ የክልሉ ም/ቤት አባላትና የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራ ተወካዮችን ያካተተ ልዑክ ቡድን በደንበል ወረዳ አራቢ ቀበሌ የማስፋፊያ ግንባታ ሲደረግለት የነበረውን የሼክ ጣሂር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መርቀው መክፈታቸው ተገለፀ።

በዚህ በአራቢ ቀበሌ የሚገኘው ይህ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ማስፋፊያ የተደረገለት ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ወጪውም በኢትዮጰያ ሶማሌ ክልል በተለይ የደንበል ወረዳ ተወላጅ ዲያስፖራዎች የተሸፈነ እንደሆነም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀምዲ አደን ከምርቃቱ በኋላ “በእንዲህ አይነቱ በክልሉ ልማትና እድገት ላይ ተሳትፎ በማድረጉ ረገድ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ወሳኝና ለክልሉ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን በጉልህ የሚያሳይ ሲሆን፤ የወዳው ተወላጅ ዲያስፖራዎች በክልሉ መስረተ ልማትና እድገት የድርሻችሁንን እየተወጣችሁ ስለመሆኑም በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፤ በተጨማሪም በአራቢ ቀበሌ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና ማስፋፊያ በተደረገለት በዚህ የሼክ ጣሂር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ምርቃት ላይ ለማስመረቅ በመገኘቴም የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ።”ሲሉ ም/ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በበኩላቸው የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች መንግሥት ከሚያከናውናቸው የመስረተ ልማትና እድገት ጎን በመሆን እነሱም በክልሉ ልማትና መልካም አስተዳደር የሚያደርጉት ተሳትፎ ቀላል የሚባል እንዳልሆነና ይንንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማሳሰባቸውም በክልሉ ጤና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይቶሬት ገልጿል።