የኢ.ሶ.ክ ዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮ ከተለያዩ የዓለም አገራት መጥተው በጅግጅጋ ለሚገኙ ዲያስፖራዎች የጾም አፍጥራ ግብዣ መደረጉን ተገለጸ

ጅግጅጋ (cakaaranews)እሁድግንቦት 19/2010.የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮው ያዘጋጀው የጋራ የጾም መፍቻ ዝግጅት ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ እናት አገራቸው በመምጣት አሁን በክልሉ ላለው የሠላም ፣ ልማት እና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የልማት ተሳታፊ በመሆናቸው የምስጋና ፕሮግራም እንደሆነም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮ ከተለያዩ የዓለም አገራት መጥተው በአሁኑ ወቅት በጅግጅጋ ከተማ ለሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች በጋራ ጾም የሚፈቱበት የግብዣ ፕሮግራም ማዘጋጀቱ ገልጸዋል።

በዚህ የረመዳን ጾም በጋራ ጾማቸውን እንዲፈቱ የክብር የጾም መፍቻ ፕሮግራም ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከአሜሪካ፤ከአውሮፓ፤ከኤሲያና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ተወላጅ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዲያስፖራዎች ተገኝተዋል።በመድረኩ ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት በኢ.ሶ.ክ ፕሬዝዳንት የህዝብ ቅሬታ አፈታት አማካሪና የክልሉ የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲረዛቅ ሰሃኔ ንግግራቸውን የጀመሩት ተወላጅ ዲያስፖራዎቹ እያደረጉ ባለው የሠላም ፣ የልማት ፤የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተሳትፏቸው እንዲሁም በክልሉ ባለው ዕድገት ላይ ተወላጆቹ ኢንቨስት እንዲያደርጉና እንዲያለሙ የማድረጋቸውን ትልቅ ጥረት በማድረጋቸውን አመስግኗል።  በቅድሚያ በዚህ በተቀደሰና በተባረከ የረመዳን ጾም ወቅት ከእናንተ ጋር አብረን የጾም አፍጥራ ዝግጅት ላይ በመገኘቴ በራሴና በዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮ ሥም የተሰማኝን ደስታ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፤ ሌላው በድጋሚ ያስደሰተን ነገር ቢኖር ከተለያዩ የዓለም አገራት ይህንን ያህል ተወላጅ ዲያስፖራ በአንድ  አስተሳሰብና አላማ በሃገራቸው ባለው ሠላም እና ልማት መልካም አስተዳደር ላይ የራሳቸውን ድርሻ ለመውጣት እንዲሁም የትውልድ ሃገራቸውን ለማልማት ብሎም ለመጠየቅ በፈለጉት ጊዜ መጥተው ሊያዩን በመቻላቸውና በመፍቀዳቸው ከልብ እናመሰግናቸዋለንብሏል።

በጋራ ጾም መፍቻ ዝግጅቱ ላይ የታደሙት የተለያዩ ተወላጅ ዲያስፖራዎች የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮው አክብሮ ይህንን ዝግጅት አዘጋጅቶ በመጥራቱ እና በማሰባሰቡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት እያደረገ ባለውም ዘርፈ ብዙ የልማት እና የእድገት ተግባራት ላይም በቀጥታ ተሳታፊ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል። ከእንግዶቹ መካከል ይህንን ሲናገሩ በመጀመሪያ ይህንን የመሰለ የጋራ የጾም አፍጥራ ዝግጅት ያደረጉልንን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮን በራሴ እና ከተለያዩ የዓለም አህጉራት በመጡት ተወላጅ ዲያስፖራዎች ሥም ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እኛ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ምን ጊዜም ቢሆን በክልላችን ልማት እና የክልሉ መንግሥት ጎን እንደምንቆም ልማትንም እንደምንደግፍ ለመግለጽ እወዳለሁ ክቡራንና ክቡራት  በድጋሚ በራሴ እና በተወላጅ ዲያስፖራዎች ሥም መናገር የምፈልገው የክልሉ መንግሥት እንዲሁም የክልሉ መሪ ፓርቲ ኢሶህዴፓ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለልማቱና ለህዝቡ ተጠቃሚነት በማሰብ የሚያካሂዳቸውን ተሃድሶን እንደምንደግፈውና ለእነዚህ ሁሉ የልማት ስኬቶች ደግሞ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው በዚህም አጋጣሚ ድጋፋችንን ልንገልጽላቸው እንወዳለንብሏል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎቹ ዛሬ ላይ በክልሉ እየተከናወኑ ባሉ ሠላም ልማት እና መልካም አስተዳደርና እንዲሁም በክልልም ሆነ አገር ደረጃ በሚደረጉ ልማትና ኢንቨስትመንት ላይ ያላቸው ተሳትፎ በጥንካሬነት ሊጠቀስ የሚችለው የክልሉ መንግሥት በውስጥና በውጭ አገራት የሚያደርጋቸው መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንደሆኑ ተገልጿል።

የቀብሪደሃር ከተማ መስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች 12 የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች አስመርቀዋል

ቀብሪዳሃር (Cakaaranews) እሮብ፤ግንቦት 15/2010 .የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት ለክልሉ ህዝብ አስፈላጊውን የመሠረተ ልማት ግንባታ በሁሉም አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሌት ተቀን በትጋት እየሠራ ይገኛል። በዚህም የክልሉ መንግሥት የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮችን በመቅረፍ በክልሉ የሚገኙትን ወረዳዎች እና ቀበሌዎች እርስ በእርስ በማስተሳሰር እንዲሁም ህብረተሰቡ በእለት ተእለት እንቅስቃሴ ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ላይ ትስስር እንዲኖራቸው ክልሉ የመንገድ አገልግሎት ተደራሽነትን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ላይ ይገኛል።

በመሆኑም የቀብሪዳሃር ከተማ መስተዳደር 12 ግንባታቸው የተጠናቀቀ የድንጋይ ንጣፍ (ኮብል ስቶን) መንገዶች   የቀብሪዳሃር ከተማ መስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት የቀብሪዳሃር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዩሱፍ ሀሰን አስመርቋል። በምረቃት ሥነ ስርዓት ላይ የከተማው ከንቲባ አቶ ዩሱፍ ሀሰን 12ቱን የኮብል ስቶን መንገዶች ግንባታ ለማጠናቀቅ የወጣው ወጪ 9.5 ሚልዮን ብር እንደሆነ ፣ ለ520 የከተማዋ ነዋራዎችም የሥራ እድል እንደፈጠረላቸው እንዲሁም መንገዶቹም ጥራት ባለው መልኩ እንደተሠሩና ቀደም ሲል በከተማው የነበረው የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮችን እንደሚቀርፍም ገልጿል።

በመንገዶቹ ግንባታ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውና በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማው ነዋሪዎች  በበኩላቸው በመንገዶቹ መገንባት የተሰማቸዉን ደስታ በመግለፅ ፣ የመንገዶቹ መገንባት በከተማው ህብረተሰብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴና በአከባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ትልቅ እምርታ እንሚያመጡ አክለው ተናግረዋል።

 

 

 

የቀብሪደሀር ከተማ አስተዳደር ከወጣቶች ጋር በሠላምና ልማት ዙሪያ ተወያየ

ቀብሪደሀር(Cakaaranews)እሁድ፤ግንቦት 12/2010 ዓ.ም በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ  የተገኘውን የሠላም ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማጠናከር ሁሉም የቀብሪሀደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች የተሳተፉበት የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ በቀብሪሀደር ከተማ ተካሄደ። በመድረኩም ላይ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ በድሪ ዩሱፍ የዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴን መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ኪፋህ መዓሊን የጅግጅጋ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ካሚል አብዲላሂ ሃይቤ እና የቆራሄይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ በተጨማሪም የቀብሪሀደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዩሱፍ ሀሰን እንዲሁም ሌሎች የክልልና የዞኑ ከፍተኛ አመራር አካላት ተገኝተዋል።

በተጨማሪም መድረኩን የመሩት የኢ.ሶ.ክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ በድሪ ዩሱፍ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በሁሉም የልማት ዘርፎች የተከናወኑትን ስኬቶች ማስቀጠልና በአሁኑ ወቅት ክልሉ ለደረሰበት የልማት ጎዳ የክልሉ ወጣቶች ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ በመግለፅ  ክልሉ ያሳከቸዉን የልማት ሥራዎች በአንዳንድ የክልሉን ዕድገት በማይወዱ አካላት እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ የክልሉም ሆነ የቀብሪሀደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በንቃት መከላከል እንዳለባቸው ጥሪያቸዉን አቅርበዋል፡፡

አያይዞም በቀብሪደሀር ከተማ አስተዳደር በጥቂት ዓመታት ከተከወኑ የልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ቀብርደሀር ዩኒቨርሲቲ ፣ የቀብሪደሀር ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ፣ የሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮችም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ም/ቢሮ ኃላፊው አቶ በድሪ ዩሱፍ ።

በሌላ በኩል በክልሉ በተለያዩ የሀላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ የአመራር አካላት የኢ.ሶ.ክ. ባለፉት ዓመታት በሁሉም የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስኬቶችን በመጎናፀፍ ክልሉ በአሁኑ ጊዜ በልማት ጎዳና ላይ መሆኑን በመግለፅ ፤ እንዲሁም ክልሉ ያሳከቸዉ የልማት ሥራዎች የማይዋጥላቸው የተለያዩ ፀረ-ልማት አካላት ለክልሉ የልማት ሥራዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ መከላከል እንዳለባቸው ለወጣቶቹ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ አያይዘውም ኃላፊዎቹ በክልሉ የተጀመረዉን የሠላም ፣ የልማት ፣ የመልካም አስተዳድርና የህዳሴው የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖራቸው የቀብሪዳሃር ወጣቶች የድርሻቸዉን እንዲወጡና ቀጣይነታቸዉን እንዲያረጋግጡ ጥሪያቸዉን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የቀብሪዳሃር ከተማ አስተዳድር ወጣቶች በበኩላቸው በክልሉ እየተከናወነ ያለዉን የሠላም ፣ የልማት ፣ የመልካም አስተዳድርና የህዳሴውን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉና ከክልሉ መንግሥት ጎን ቆመው የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡ አያይዞም ወጣቶቹ በክልሉ እየተመዘገቡ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የማይዋጥላቸው የተለያዩ ፀረ-ልማት ሀይሎችን እንዲሁም በክልሉ የልማት ሥራዎች ላይ እንቅፋት ለመሆን የሚሞክሩ አካላትን እንደሚከላከሉ እና እንደሚዋጉም ተናግረዋል፡፡ 

የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የከተማውን ዋና ዋና መንገዶች እድሳት እንደሚያደርግና አዳዲስ መንግዶችም እየሠራ መሆኑን ገለጸ

ጅግጅጋ(Cakaaranews)እሮብ፤ግንቦት 15/2010ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት የክልሉን ዞኖችና ከተሞች የሚያስተሳስሩ መንገዶችና ትላልቅ ድልድዮች በአፋጣኝ የሚሠራበት ፖሊሲና ስተራቴጅዎች ነድፎ በክልሉ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞችና በዞኖች ገጠር አከባቢዎች የመንግድ መሠረተ ልማት አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

በዚህም የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዲአዚዝ መሀድ “በከተማው ዳርቻ ወይንም በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኙ ሰፈሮች አዳዲስ የውስጥ ለውስጥ እና ረጃጅም የአስፋልት መንገዶች ግንባታ በክልሉ ኮንስትራክሽን ፣ ግዢና ልዩ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ እየተከናወኑ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም በጅግጅጋ ከተማ የሚገኙ የ11 ፣ የ12 እና የ17 ቀበሌዎችን የሚያስተሳስር የአስፋልትና የድንጋይ ንጣፍ (ኮብል ስቶን) መንገዶች እድሳትና ጥገና እየተሠራ ከመሆኑም ባሻገር በከተማው ዳርቻ ላይ የሚገኘው የሼክ ኑር ኢሴ ሰፈርም አዲስ የአስፋልት መንገድ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ገልጿል።

በመጨረሻም በጅግጅጋ በሼክ ኑር ኢሴ መንገድ አካባቢ የሚሠሩ የታክሲ አሽከርካሪዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች የክልሉ መንግሥትና የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደሩ በከተማው ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ሰፈሮች አዳዲስ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በመሥራቱ ከአሁን በፊት የነበሩትን የትራንስፖርት ችግሮች እንደሚቀርፍና  የክልሉ መንግሥት ለመንገድ መሠረተ ልማት በሰጠው ትኩረት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስመረቀ

ቀብሪበየህ(cakaaranews) )ቅዳሜግንቦት፣ 11 2010ዓ.ም የፌዴራሊዝምም ሆነ የክልል መግንስት የታችኛው አቅመ አናሳ ህብረተሰብ ክፍሎችን የመሠረተ ልማት እጥረት ለመቅረፍ ከተነደፉት ሜጋ ፕሮጀክት እቅዶች ፣ ስትራቴጅዎችና ፖሊሲዎች አንዱና ዋነኛው  ዘመናዊ የቤቶች ልማት መርሃ ግብርና ጥራት ያላቸውን የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በማፋጠን ለተጠቃሚዎች አገልግሎት ማብቃት ነው። በዚህም በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሚመራ የክልሉ አመራር አካላት በቀብሪበያህ ከተማ የተገነቡ ዘጠኝ የሚሆኑ የመኖርያ ቤቶችን አስመርቀዋል።

በተጨማሪም የቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙክታር መሀመድ አብዲ በ2010 በጀት ዓመት በቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር የተገነቡትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስመረቃቸውና ለከተማ አስተዳደሩ አቅመ አናሳ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ በማድረጋቸው እጅግ ደስተኛ ከመሆናቸውም በሻገር በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ወቅት በርካታ የሀገሪቱና የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል። አያይዞም የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች በእጣ መልክ እንዲታደሉ ከንቲባ አቶ ሙክታር መሀመድ  ገልጿል።

በ2010 በጀት አመት በቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር የተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በጥራትና በዘመናዊ መልኩ ተገንብተው ለታቀደለት የከተማ አስተዳደሩ የታችኛው ማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ተደርገዋል ያሉት የቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘምዘም ሁሴን አብዲ ናቸው።

በመጨረሻም በቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር የተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በታደሉበት ጊዜ ተጠቃሚዎቹ በጥራትና በዘመናዊ መልኩ የተገነቡ ቤቶችን በማግኘታቸው በጣም ደስተኛ ከመሆናቸውም ባለፈ ለክልሉ መንግስት የላቀ ምስገናቸውን አቅርበዋል።

 

Amharic News 20_10_10


Amharic News 19_10_10


Amharic News 17_10_10Amharic News 16_10_10Amharic News 15_10_10


Amharic News 14_10_10


Amharic News 13_10_10Amharic News 12_10_10Amharic News 11_10_10