በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ 29 ለሚሆኑ ጥንዶች ባልተለመደ መልኩ ቅልጥ ያለ የሠርግ ድግሥ ተደረገ

ጅግጅጋ (Cakaaranews) አርብ ሚያዝያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ከዘመናት በፊት የሶማሌ ማህበረሰብ ባህል እና ልምድ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውጭ የገጠማቸውን የረሃብ አደጋ ለመከላከል የሞቱ እንስሳትን ወይም በክት በልታችኋል ተብለው የገቦያ ጎሳ አባላት ከሌላው የሶማሌ ጎሳዎች እንደተገለሉ በአፈ ታሪክ ይነገራል። በዚህም አፈታሪክ ምክንያት ለዘመናት በሶማሌ ጎሳዎች መድልኦ እና መገለል ደርሶበት የሥነ ልቦና ችግር በገቦያ ማህበረሰብ ላይ እንደደረሰም ይታወቃል። የገቦዬ ጎሳ ማህበረሰብ ከሌላው የሶማሌ ጎሳዎች በሃይማኖት ፣ በባህል እና በወግ አንድ ሆኖ ሳለ በደረሰበት መገለል የበታችነት ስሜት ተፅዕኖ በማህበረሰቡ ላይ ከማምጣቱም በተጨማሪ ማህበረሰቡ አነስተኛ የሥራ ዓይነት አድርጎ በሚወስደው የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ህይወታቸውን ማቆየት ችለዋል።

የገቦያ ማህበረሰብ ልክ እንደሌሎቹ የሶማሌ ጎሳዎች ከተለያዩ ጎሳዎች ጋር መጋባት የማይችሉ እንደነበሩና ገቦዬዎች እርስ በእርሳቸው ትዳር የሚመሰርቱበት ምክንያትም የሌላው የሶማሌ ጎሳ ልጆች በጋብቻ ከገቦያ ጎሳ ልጆቸ ጋር እንዲተሳሰሩ ባለመፈለጋቸውም ነው። ይህንን በገቦያ ጎሳ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጫና እና መገለል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድም የታሰበው ጠንካራ አቋምና የክልሉ መንግሥት ዕቅድ ዛሬ ላይ መልካም ውጤት እያመጣ መሆኑንም መረጃዎቹ ያመላክታሉ። ይህ የገቦያ ማህበረሰበ በሥራ የሚናቁና ከአሁን በፊት የትምህርት ዕድል ያልተሰጣቸው በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ለገቦያ ማህበረሰብ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበትን በርካታ መድረኮች በማዘጋጀት ፤ እንዲሁም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አብዲ መሃሙድ ኡመር የተወሰደ ጠንካራ አቋም ፣ ጥረት እና ተነሳሽነት ከዚህ ቀደም በገበያ ጎሳ ማሀበረሰብ ላይ ይደርሱ የነበሩ አላስፈላጊ የሆኑ የንቀት ቃላትን እንዲወገዱ እንዲሁም በትልልቅ የሥራ ድርሻ ላይ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፈር ቀዳጅ የሆኑ የጎሳው አባላትን የሞራል ጥበቃ እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ መናገራቸውን ይታወሳል።

በተጨማሪም ክቡር ፕሬዝዳንቱ የገቦያ ማህበረሰብን በሶማልኛ ቋንቋ የተለያዩ ስያሜን በመስጠት ትንኮሳን የሚያደርሱባቸውን የሌላ ጎሳ አባላት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከዚህ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሳይናገሩ ያለፉበት ጊዜ አልነበረም። በተፈጥሮ ችግር የሌለባቸውን እነዚህን ጎሳ ከሚተነኩሱባቸው የቃላት አጠቃቀም ለምሳሌም “ሚድጋን” የሚለው ቃል ጥንት ለእንስሳት አደን ሲጠቀሙበት የነበረ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ቀስት ማስቀየስ” የሚል ሲሆን “ገቦየ” የሚለውም “የቀስት መያዣ” ሲሆን “ቱልማል” የሚለውም “ቀጥቃጭ ወይም አንጥረኛ” የሚሉ ትርጉሞች እንዳላቸው እና አብራርተዋል። በሌላ በኩል በቅርቡ በአፍዴር ዞን በራሶ ወረዳ በተካሄደው 11ኛው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ እና መንግሥት የጋራ ምክክር መድረክ በሶማሌ ጎሳዎች መካከል አንዱን ጎሳ ከሌላው ጎሳ ማበላለጥ ወይም ማስተናነስ አላስፈላጊ እንደሆነ እና በእምነት ፣ በባህል እና በወግ በመቻቻል እንዲሁም በመከባበርና በህገ መንግሥቱን መሠረት ባላደረጉ አስተሳሰቦች በእነኚህ ጎሳ አባላት ላይ የሚደርሰውን የንቀት የቃላት አጠቃቀም ጨምሮ ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች መቆም እንዳለባቸው በፅኑ ዕምነት በማፅደቅም ነበር። በዚህም የክልሉ ባለሃብቶች ፣ የመንግሥት  እና የግል ሠራተኞች እንዲሁም በክልሉ በልማት ሥራዎች  እየተንቀሳቀሱ ያሉ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ባደረጉት ከፍተኛ የገንዘብ መዋጮ ከገቦያ ጎሳ ሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም ከሌሎቹም ጎሳዎቸ እንዲሁ ሁለቱም ፆታዎች የቆዩ ጎጂ ልማዶችን ከማስቀረት አንፃር በሌሎች ክልሎች ያልታየ እንዲሁም የዘመኑ ሰርግ ሥነስርዓት በመናዊና ፈር ቀዳጅ በሆነ መልኩ ቅልጥ ባለ የሠርግ ዝግጅት እንዲአደረጉ ተደርገዋል። በዚህም መሰረት 29 ጥንዶች በምድረ ሶማሌ እንዲሁም ኢትዮጵየያ ተሰምቶም ሆነ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ደማቅ የሠርግ ድግሥ ተደርጎላቸዋል። ልዩ ዝግጅቱም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መቀመጫ በሆነችው ጅግጅጋ ከተማ በአርበኛው ሰይድ መሃመድ አዳራሽ የአብዛኛውን ሶማሌ ቀልብ በሳበ መልኩ ነበር የተዘጋጀው።

በዚህም መሰረት በጅግጅጋ ከተማ ታሪክ የተባለለት የዚህ ሠርግ ድግሥ ታዳሚዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አብዲ መሃሙድ ፣ የክልሉ ም/ፕሬዝዳንቶች ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ፣ የዕምነት አባቶችና ሴቶች ፣ የሃገር ሽማግሌዎች ፤ወጣቶች እና የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት በተገኙበት እንዲሁም በሶማሌኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ አንድነትን ፣ መቻቻልን እና እኩልነትን በፈጠረ እንደሁም ባህላዊ ስርዓትን በለበሰ መልኩ እንድካሄድ ተደርገዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ የሶማሌ የሠርግ እና ባህላዊ ጭፈራዎች እና ሙዚቃዎች እንደ “ዳንቶ” ያሉ ጭፈራዎች እንዲሁም በሶማሌ የሠርግ ሥነስርዓት ልዩ እና ድንቅ የሚያደርገውን የፖሊስ እና ዳኝነት የእንቆቅልሽ ጥያቄና መልስ ውድድርም በማካተት ታዳሚዎቹን ባስደሰተና ባዝናና መልኩ ማዘጋጀቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

በተጨማሪም በዝግጅቱ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሃሙድ ኡመር “ይህ የሠርግ ሥነስረዓት በኢትዮጵያ ሃገራችን በእስልምናም ሆነ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች ፣ በባህላችን እንዲሁም የምንተዳደርበትን ህገ መንግሥት መሰረት ያላደረገ ሲወርድ እና ሲዋረድ በመጣ ጎጂ ልማድ በዘር ወይም በጎሳ መበላለጥ ከአሁን በኋላ እንዳይኖርና አንዱ የጎሳ አባል ሌላውን እንዲያከብር የመቻቻል እና የመከባበር ሃገር እንድትኖረን ትርጉም የማይሰጡ የመናናቅ አመለካከቶችን እንዲወገዱ” መልዕክታቸውን አስተላልፏል። አያይዘውም በአፍሪካ ቀንድ እና በአምስቱም አህጉራት ለሚኖሩ የሶማሌ ህዝቦች በራሳቸው ፍላጎት እና ምርጫ ከተለያዩ የሶማሌ ጎሳዎች እና ከገቦያ ጎሳ አባላት ጋር ጋብቻቸውን ያደረጉት 29 ጥንዶች እንደ ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ በማህበረሰባቸው ውስጥ የሚታዩን ጎጂ ልማዳዊ አመለካከቶች እንዲያስወግዱ አሳስበዋል ፕሬዝዳንቱ። በተጨማሪም ሶማሌኛ ቋንቋ የሚናገሩ ጎሳዎች ሁሉም የሰው ልጅ ፍጡር እኩል እስከ ሆነ ድረስ አንዱን የበታች ሌላውን የበላይ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንደሌሉም ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል። በመጨረሻም ክቡር አቶ አብዲ መሃሙድ በጋብቻ የተጣመሩትን ጥንዶች ትዳር የተባረከ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የዚህ ሠርግ ሥነስርዓትም ልዩ ዝግጅት በክልሉ ዘርፈ ብዙ የሰላም ፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች የተከናወኑበት ወቅትና እንዲሁም በቅርቡ የተሰየሙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አቶ አብይ አህመድ የመጀመሪያ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በከሊ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር የሃገራችንን ሉዓላዊነት እና ዳር ድንበር የጠበቁ የኢትዮጵያ ሶማሌ ጀግኖች በአርበኛው ሰይድ መሀመድ አብዲሌ እና ደጃዝማች ኡመር ሰመተር እንደሚኮራባቸው በማስረገጥ ነበር እንዲሁም ኢትዮጵያ ካለነርሱ የማትታሰብ እንደሆነች በተናገሩበት ወቅት የሰርጉ መገጣጠም ኢትዮጵያ በልጆቿ እንደምትኮራ አረጋግጧል።