በዶ/ር አብዱልመጂድ መምህራን ኮሌጅ ለ23ኛ ጊዜ የተማሪዎች ምርቃት ላይ የኢ.ሶ.ክ. ፕሬዝዳንት ተካፈሉ

ጅግጅጋ(Cakaranews) እሁድ፤ሰኔ 03/2010. በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት የዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴን መታሰቢያ መምህራን ኮሌጅ ለ23ኛ ጊዜ ያስመረቃቸውን ተማሪዎች በጅግጅጋ ከተማ በሰይድ መሀመድ መሰብሰቢያ አዳራሽ ደማቅ የምረቃ ሥነ-ስርዓት አድርጎላቸዋል።

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይም የኢ.ሶ.ክ.መ.ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የኢ.ሶ.ክ.መ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ፣ የኢ.ሶ.ክ.መ ም/ፕሬዝዳንትና የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀምዲ አደን፣ የክልሉ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ማጂዳ መሀመድ፣ የዶ/ር አብዱልመጂድ መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ኪፋህ መዓሊን፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራህም አደን እና  የተመራቂ ተማሪዎች ወላጆች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል። የእለቱ ክቡር እንግዳ የነበሩትና መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢ.ሶ.ክ.መ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ዛሬ ዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴን መታሰቢያ  መምህራን ኮሌጅ ለ23ኛ ጊዜ ያስመረቃቸው መምህራን በክልሉ እየተከናወነ ላለው ዘርፈ-ብዙ የልማት ተግባራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልጿል።

በተያያዜም የዶ/ር አብዱልመጂድ መታሰቢያ መምህራን ኮሌጅ ተማሪዎችን ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት በክልሉ ጥራት ያላቸው መምህራን ለማፍራት የኮሌጁ አመራርና መምህራኑ ለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት በማመስገን ተመራቂ ተማሪዎቹ ከዚህ የቀሰሙት ትምህርትና እውቀትን ለክልሉ ማህበረሰብ እንዲያካፍሉና ተመራቂ መምህራኑ በቀጣይ የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች የበለጠ የትምህርት ጥራትን በሃላፊነት እንዲሰጡ እንዲሁም ለክልሉና ብሎም ለሀገሪቱ ህዝብ በማገልገል የዜግነት ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ክቡር ፕረዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራህም አደም መሀድ በበኩሉ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ባለፉት አስርት አመታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ከመሆኑም ባሻገር የኢ.ሶ.ክ. መምህራን ኮሌጆች የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት በአጠቃላይ በክልሉ ትምህርት ተደራሽነት ላይ አመርቂ ውጤቶች ማስመዝገቡን በመግለጽ አሁን የዶ/ር አብዱልመጂድ መምህራን ኮሌጅ ለ23ተኛ ጊዜ ያስመረቃቸው አስተማሪዎች በክልሉ መልካም ሥነ-ምግባርን የተላበሱና ብቁ ዜጎችን ለማፍራት  እንዲችሉ እንዲሁም የሃገራችንን መምህራን ሥነ-ምግባር በጠበቀ መልኩ ህዝቡ የጣለባቸውን አደራ በኃላፊነት የበኩላቸው እንዲወጡ አሳስቧል።

በተመሳሳይም የዶ/ር አብዱልመጂድ መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ኪፋህ መዓሊን በበኩሉ ኮሌጁ ዛሬ በሁሉም ጾታ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያስመረቃቸው መምህራን ብዛት 382 መሆኑን በመጥቀስ ተመራቂዎቹ፤ የመምህራን ሥነ-ምግባርና ሙያን የሚያሳንሱና የመምህራን ሥራ ከሚያንቋሽሹ  እንደ ሙስና፣ ወገንተኝነት፣ ብሔርተኝነት እና ከመሳሰሉት አላስፈላጊ ተግባራት እንዲቆጠቡና ለተጣለባቸው ኃላፊነት የበኩላቸውን እንዲወጡ አስምሮበታል።

በተጨማሪም የኢ.ሶ.ክ.መ. ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ በዶ/ር አብዱልመጂድ መምህራን ኮሌጅ ለ23ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው መምህራን መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ለተመረቁት መምህራን የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማት አበርክቶላዋል።

በመጨረሻም ተመራቂ መምህራኑ ከብዙ ጥረት በኋላ በመመረቂያቻው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመገኘታቸው በጣም መደሰታ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን በቀጣይም የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል።